የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር የኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚያስችሉ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት ባገኘው ገንዘብ የገዛቸውን 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶች ለሕክምና ተቋማት ማስረከብ ጀመረ።
የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ተስፋዬ፣ ማኅበሩ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት የሆነውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በተለይ በእናቶች እና ሕፃናት ዙሪያ ለሚሠሩ ሚድዋይፎች የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል። ድጋፉም የፊት ጭምብል (N95 Mask) ፣ የንጽሕና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፣ የፊት መከላከያ ጭምብል (Face Shield)፣ ሙሉ ልብስ (Water proof Gown) ያካተተ ነው።
ማኅበሩ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚድዋይፎች ቀን ምክንያት በማድረግ ድጋፉን በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ለሚገኙ የሕክምና ባለሞያዎች ማስረከብ ጀምሯል። በቀጣይም በዘጠኙም ክልሎች እና በሁለቱም ከተማ መስተዳድሮች ለሚገኙ የሕክምና ተቋማት እንደሚሰጥ አቶ የሺጥላ ጠቁመዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ሕፃናት ዳይሬክተር ዶ/ር መሠረት ዘላለም ማኅበሩ ላደረው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። ዳይሬክተሯ የእናቶች እና ሕፃናት ሕክምና ትኩረት እንደሚሻ ገልጸው፣ በኮቪድ-19 ምክንያት የወሊድ፣ የቤተሰብ እቅድ እና የጨቅላ ሕፃናት ሌሎች የጤና አገልግሎት እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል። በመሆኑም ሁሉም መሰረታዊ አገልግሎት ሳይስተጓጎሉ በተገቢው ሁኔታ እንዲሰጡ ድጋፍ እንዲሚያደርጉም ዳይሬክተሯ ጠይቀዋል።